አስተምህሮ

አዕማድ እምነቶች (አስተምህሮ)​

Apostle Born Ministries የእምነት መሠረት በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኳ የተጻፈው የመጀመሪያይቱ የሐዋርያት ቤተክርስቲያን እምነት ነው፡፡ ስለዚህ Apostle Born Ministries ጥንታዊያኑ ታሪካዊያኑ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት ያወጧቸውን፡- የሐዋርያት፣ የኒቂያ፣ የአትናቴዎስና የኬልቄዶን የእምነት መግለጫዎች ተቀብለው በየዘመኑ የተነሱ ተሐድሶዓውያን ወደ ቀደመው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነትና አስተምህሮ ለመመለስ ያደረጉትን ጥረቶች አካትተው የቆሙ ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት Apostle Born Ministries “አምስቱ ብቻዎች” በመባል የሚታወቁትን “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” “ክርስቶስ ብቻ” “በጸጋ ብቻ” “በእምነት ብቻ” እና “ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ” እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የሚጠቀሰው ‘የአማኞች ሁሉ ክህነት’ የተባለውን አስተምህሮ ይቀበላል፡፡

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት Apostle Born Ministries ዋና ዋና የእምነት ምሶሶዎች መሠረታዊያን በመሆናቸው ወሳኞችና ዐበይት አስተምህሮ ናቸው ብለን እናምናለን እናስተምራለን፡፡

አዕማድ 1: መጽሐፍ ቅዱስ – ቃለ እግዚአብሔር

Apostle Born Ministries ስድሳ ስድስቱን የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር እስትንፋሳዊ ቃል፤ የአማኞች የእምነታቸውና የምግባራቸው ዋና መመሪያና የመጨረሻ ባለሥልጣን እንዲሁም ማዕከል እንደሆነ ያምናል፤
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤የእግዚአብሔር መገለጥ ነው፡፡ በቅዱሳን ሰዎች አማካኝነት የተጻፈ ቢሆንም በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና ተቆጣጣሪነት የተጻፈ ነው፡፡ ስለዚህ በውስጡ የተካተቱት እርስ በርስ የተያያዙትና የሚቀባበሉት ሁለቱም ኪዳናት የሚያስተምሩት ትምህርት ስህተት አልባና የማይሻር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰው የአእምሮ እውቀትና አመክንዮ ችሎታ በላይ ከግለሰቦች ገጠመኞችና ልምምዶች በላይ እንዲሁም ከቤተክርስቲያን ወግና ልምምድ በላይ የላቀ ሥልጣን ያለው፤ ሊቀነስበት ወይም ሊጨመርበት ያልተፈቀደ፤ ቤተክርስቲያንን በእውነቱ ሥልጣን የሚመራ ቃል ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የታሪክ ሂደት ልዩ ልዩ የትርጓሜ ወይም የሥነ-አፈታት መስመሮች ቢከሰቱም እውነተኛ የአተረጓጎም ሂደት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈበትን ዐውድ ያገናዘበ ከአሁኑ ዘመን ጋር ያለውን ተዛምዶ ያጤነ እና በመንፈስ ቅዱስ አብርሆት የሚደገፍ መሆን እንዳለበት Apostle Born Ministries እናምናለን እናስተምራለን፡፡

(ምሳ 30፡6፤ ሉቃ 4፡18-2፤1ጢሞ 5፡18፤ 2ጢሞ 3፡16፤ 2ጴጥ 1፡ 20-21፤ 2ጴጥ 3፡15-16፤ ዕብ1፡1-2 ዕብ 4፡12፤ ራዕ.22፡18-19፤)

Apostle Born Ministry USA

አዕማድ 2: እግዚአብሔር አሀዱ ወሥሉስ አምላክ

እግዚአብሔር አሀዱ ወሥሉስ አምላክ
Apostle Born Ministries በሦስት አካላት (persons) በሚኖር አንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ፤ በእግዚአብሔር ወልድ፤ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያምናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረቱ በሆነው ርቱዕ ክርስትና የሚስጥረ ሥላሴ አስተምህሮ መሠረት እግዚአብሔር አንድ ነው፡፡ ከዘላለም ጀምሮ፤ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ተብለው በሚጠሩ ሦስት አካላት ይኖራል፡፡ እያንዳንዱ የሥላሴ አካል ፍጹም አምላክ ነው፡፡
እግዚአብሔር በሦስት አካላት ይኖራል ስንል ሦስት አማልክት ወይም መለኮቶች አሉ ማለት አይደለም፡፡ “ሦስት የሚለው ቃል ‹ስምን› ግብርን› አካልን› የሚያመለክት ሲሆን አንድ የሚለው ቃል ደግሞ ‹ባህርይን› ‹መለኮትን› እና ‹ሕልውናን› ያመለክታል፤ ስለዚህ Apostle Born Ministries በአሀዱ ወሥሉስ አምላክ (በሥላሴ) እናምናለን እናስተምራለን፡፡

(ዘፍ 1፡26፤ ዘዳ 4፡35፤ ዘዳ.6፡4፤ 1ዜና17፡20፤ ማቴ. 3፡16፣ 28፡19፤ 1ቆሮ 8፡4-6፤ 2ቆሮ13፡14፤ 1ጢሞ 1፡12)

አዕማድ 3: የሰው ማንነት ሁኔታ

Apostle Born Ministries ሰው በእግዚአብሔር አምሳል በመፈጠሩ አምላክ በሉዓላዊነቱ በሚያስተዳድረው ፍጥረት ውስጥ ምድርን የመጠበቅና የማልማት አደራና ኃላፊነት የተቀበለ ክቡር ፍጡር እንደሆነ፤ ሰው በፍጥረቱ በዕውቀቱና በችሎታው ውስን የሆነ፤ መለኮትነት የሌለው፤መጽሐፍም እንደሚል “ከእግዚአብሔር ሕይወትና እስትንፋስ እየተቀበለ የሚኖር በእግዚአብሔር ላይ ተደጋፊ ፍጡር እንደሆነ፤ ሰው ከምድር አፈር በመበጀቱና የእግዚአብሔር እስትንፋስ በውስጡ በመኖሩ ቁሳዊም፣ መንፈሳዊም ማንነት ያለው ፍጡር መሆኑን፤ ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ወይም ትዕዛዝ ችላ በማለት የራሱን ፈቃድ በተከተለ ጊዜ በኃጢአት መውደቁና ኃጢአትም ወደ ምድር መግባቱን፤ ከዚህም የተነሳ የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ቀውስ ጠብና መለያየት፤ በሽታና ስቃይ ጭንቀትና መከራ ሞትም መከሰቱን፤ ስለዚህም የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ በኃጢአት ምክንያት በሰው ልጅ ላይ እንደደረሰ እናምናለን እናስተምራለን፡፡

(ዘፍ 1፡26-27፤ ዘፍ 2፡7፤ ዘፍ 2፡21-22፤ ዘፍ 3፡16-19፤ ኢዮብ 10፡8፤ ኢዮብ 33፡4፤ መዝ 100፡3፤ ኢሳ 42፡5፣ 45፡12፤ ኤር 27፡5፤ ሐዋ.17፡ 24-27፤ ራዕይ 4፡11)

አዕማድ 4: የሰው ልጆች ድነት (መስቀለ ክርስቶስ – የድነት ጎዳና)​

Apostle Born Ministries ሰው ከኃጢአት ዕዳ ኃይልና ቅጣት ሊድን የሚችለው ኃጢአት የሌለበት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ምትክ ሆኖ በመስቀል ላይ በፈጸመው የቤዛነት ሥራ ብቻ በመሆኑ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር ጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ እንደሚጸድቅ ያምናል፡፡
Apostle Born Ministries የሰው ልጅ በራሱ ሥራም ይሁን በሌሎች ፍጥረታት እርዳታ በኃጢአት ምክንያት ከመጣበት የእግዚአብሔር ቁጣ ሊድን ስለማይችል ድነት ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ጸጋና ምህረት መሆኑን፤የክርስቶስ መስቀል የሰው ልጅ ድነት ሙሉ ለሙሉ የተከናወነበት ቦታ እንደሆነ፤ ክርስቶስ በመሞቱና በመነሳቱ የዘላለም ሕይወት ዋስትና መገኘቱን ያምናል፡፡
Apostle Born Ministries መስቀሉ የወንጌል ማዕከል መሆኑን የመስቀሉም መንገድ የኑሮአችን መርሕና ዘይቤ እንደሆነ ማለትም በመስጠት ማግኘት የሚስተናገድበት ከሁሉ ኋላ በመሆን ፊተኛ የሚኮንበት፤በድካም ብርታት የሚገለጽበት፤ ስለዚህም በውርደት ክብር የሚለበስበት የሕይወት ቅኝት መሆኑን ያምናል፡፡
Apostle Born Ministries ሰው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን በመንፈስ ዳግም በመወለድ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚሆን፤ አዲስ ፍጥረትም እንደሚሆን፤ ከእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ ድኖ የክርስቶስን ጽድቅ እንደሚጎናጸፍ ያምናል፡፡ ይህም አዲስ ፍጥረት በጽድቅና በቅድስና የተቃኘ አዲስ የሕይወት ዘይቤ ይከተላል፡፡ በዚህ ምክንያት መጽሓፍ እንደሚያስተምረው “መንፈሱም፣ ነፍሱም፤ ሥጋውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለነቀፋ ፈጽሞ እንዲጠበቅ” በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሁለንተናው በቅዱስ ኑሮ የተመራ ሰው እንደሚሆን ያምናል፡፡
Apostle Born Ministries እንደሚያምነው ኃጢአት አመጽ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ያለመታዘዝና ሕግን የመተላለፍ ተግባርም ነው፡፡ ኃጢአት ከእግዚአብሔር አሳብና ፈቃድ ውጭ የመሆን ኑሮ ነው፡፡ የኃጢአትም ደመወዝ ሞት ነው፡ ፡ Apostle Born Ministries በክርስቶስ አምኖ ዳግም የተወለደ ሰው ኃጢአት ሊያደርግና በኃጢአት ሊኖር እንደማይገባው ያምናል፡፡ ነገር ግን አማኝ ኃጢአት ቢያደርግ በእውነተኛ ኑዛዜና ንስሐ ወደ ጌታ ቢመለስ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ እንደሚያነጻው እናምናለን እናስተምራለን፡፡

(ኢሳ 53፡1-12፤ ዮሐ 3፡16፤ ሮሜ 3፡25፣ 8፡3-4፤ ኤፌ 2፡5-6፤ 1ተሰ 4፡2፤ ቲቶ 2፡11-15፤ 1ዮሐ 1፡7-10፣ 4፡10፣ 5፡23)

አዕማድ 5: ቤተ ክርስቲያን

Apostle Born Ministries ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን በእግዚአብሔር መንፈስ ዳግም የተወለዱ አማኞች ሁሉ በሚገኙባትና የኢየሱስ ክርስቶስ አካል በሆነች በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ያምናል፡፡ ‘ቤተ ክርስቲያን’ የሚለው ቃል ትርጉም የክርስቲያን ወገን ወይም የክርስቲያን ማኅበረሰብ ማለት ሲሆን ቃሉ በቁሙ ሲወሰድ ሕንጻን የሚያመለክት ቢመስልም በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ግን ቤተ ክርስቲያን ማለት ማህኅበረ ክርስቶስ እንደሆነ ያምናል፡፡
የቤተ ክርስቲያን መሥራች እና ጀማሪዋ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ፤ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተዋጀች በመንፈስ ቅዱስ ለቤዛ ቀን የታተመች ፤ በቃሉና በመንፈሱ እየነጻችና እየታነጸች የምትገሰግስ ሠራዊት መሆኗን ያምናል፡፡
Apostle Born Ministries ቤተክርስቲያን በክርስቶስ በተገለጠው የወንጌል እውነት ላይ የቆመች ይህንኑ የመዳን ወንጌል ለዓለም ሁሉ ልታውጅ በሕይወቷም ልትገልጸው የተጠራች ባለ ተልእኮ ማኅበረሰብ እንደሆነችና አገልግሎቷን በትህትናና በቅንነት እንዲሁም በተገቢው ሥርዓት ማከናወን እንዳለባት ያምናል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ አንድነት የምትመላለስ የጌታ እራትና ቅዱስ (የውኃ) ጥምቀት በሚባሉ ቅዱስ ሥርዓቶች አንድነቷን እየገለጸች፤ የቤተ ክርስቲያን ራስ ከሆነው ከክርስቶስ በተቀበለችው ሥልጣን ምዕመኗንን እያስተዳደረችና እየመራች በዓለም ከሚገኝ ዕድፍ ራሷን እየጠበቀችና በጎ ምግባርን እያበረታታች እስከ ጌታ ምጽአት ቀን ድረስ በዚህ ምድር የምትቆይ የክርስቶስ አካል እንደሆነችም ያምናል፡፡
እንዲሁም አማኞች የአምላካቸውንና የጌታቸውን የቸርነትና የበጎ ምግባር አርአያነት ተከትለው በምድር ተንሠራፍቶ ያለውን የሰውን ልጅ መንፈሳዊ ሥነ-ልቦናዊ ቁሳዊና ማኅበራዊ ኑሮ ሥቃይ የሚካፈሉ ችግሩን ለማቅለልም በቅን ልቡና የራሳቸውን ድርሻ የሚወጡ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ያምናል፡፡ በቅዱስ ቃሉም ስለ ሥራ ትጋት የተሰጠውን መመሪያ ተቀብለው፤ በግልም ሆነ በኅብረት ለሥራ የተነቃቁ፤በታማኝነት እና በትጋት የሚያገለግሉ ሊሆኑ እንደሚገባ እናምናለን እናስተምራለን፡፡

(ማቴ 16፡18፣ 25፡34-40፤ ሐዋ 20፡28፤ ሮሜ 12፡5፣ 1ቆሮ 3፡11፣ 10፡ 16-17፤ 2ቆሮ 1፡22፤ ገላ 1፡8፣ 3፡28፤ እና 12፤ ኤፌ 4፡13፤ ያዕ.2፡14-17፤ ራዕ 1፡5፣)

አዕማድ 7: የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአትና የዓለም መጨረሻ

Apostle Born Ministries በዝግጅት፣ በንጥቀት፣በመከራው ዘመን፣ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት፣ በሺህ አመት መንግሥትና በዘላለም ፍርድ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እወስዳችኃለሁ ብሎ ተስፋ እንደሰጠን፤ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንደ ሄደ እንደዚሁ በአካል ተመልሶ ወደ ምድር እንደሚመጣ፤ የሙታንም ትንሣኤ እንደሚሆን እናምናለን። የእርሱ መምጣት የዓለም ታሪክ ፍጻሜ እንደሚሆን፤ በመጨረሻም ፍርድ ኃጥአን ወደ ዘላለም ቅጣት ሲሄዱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የሞቱት ተነስተው በመምጣቱም ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ አማኞች ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚሄዱ ይህም ለአማኞች የተባረከና በንቃት ሊጠብቁት የተገባ ተስፋቸው እንደሆነ እናምናለን እናስተምራለን፡፡

(ማቴ.24፡36-42፤ ዮሐ.14፡1-3፤ ሐዋ.1፡11፤ 1ተሰ.5፡2፤ ራዕ.19፡11-16፤ 20:11-15 22:12-15 ዩሃ14፥1-3 1ተሰ4፥13-18 1ተኛ3፡12-13 ራዕ20:4 ማቴ25፡40-42)

አዕማድ 6: ቅዱሳን ኪሩቤሎች እና ቅዱሳን መላዕክት፤ የወደቀው ኪሩቤል(ሰይጣን) እና የወደቁ መላእክት

Apostle Born Ministries እንደሚያምነው ቅዱሳን ኪሩቤሎችና ቅዱሳን መላእክት መንፈሳውያን ፍጥረት ሲሆኑ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ በሰማይና በምድር ላይ የእርሱን ዓላማ የሚያስፈጽሙ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ኪሩቤሎቹ በዙፋኑ ዙሪያ ያሉና የሚጋርዱ፣ የሚያመልኩ በፍርድ ጊዜም የሚገለጡ፣  እንደሆኑና በአፈጣጠራቸውም ከመላእክት የተለዩ መሆናቸውን፤ መላእክቱ ደግሞ የሚያምኑትን ቅዱሳን ሰዎች ለመርዳት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚላኩ ከሰው ልጆች ዕውቀትና ችሎታ በላይ ኃይል የተሰጣቸው በአምላክ ፊት መልዕክት ለመቀበል የሚቆሙ ፍጥረት መሆናቸውን፡፡

የወደቁ መላእክት የተባሉት የጨለማው ዓለም ገዢ በተባለው በመሪያቸው በዲያቢሎስ ወይም ሰይጣን አለቅነት የሚንቀሳቀሱ የክፋት መንፈሳዊያን ሠራዊት መሆናቸውን፤ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ከዚህ የጨለማ ሠራዊት ጋር በብርቱ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሲሆን “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ባለው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብርታት ድል በመንሳቱ እንደምንዞርና እንደምንቀጠቅጥ እናምናለን እናስተምራለን።

(ማቴ. 28፡2-7፣ 18 ፤ ሉቃ.9፡1፣ 10፡17-20፤ ኤፌ.6፡10-18፤ ቆላ.1፡16፤ 1ጢሞ.3፡16፤ ዕብ.1፡14፤ 1ጴጥ.5፡8-9፣ 2ጴጥ.2፡4፣ 11፤ ይሁዳ 6 ያዕ.4፡7)መዝ104:1-4 ሕዝ28፡13-15 ራዕ5:11  ሉቃ10:18-20)

አዕማድ 8:ጋብቻ(ትዳር) 

Apostle Born Ministries ጋብቻ በተቃራኒ ፆታዎች ብቻ ማለትም በተፈጥሮ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም ክቡር የአንድነት ኪዳን መሆኑን፤ ተጋቢዎችም በዋናነት መለኮትንና የመለኮትን ፈቃድ በማስቀደም በፍቅርና በታማኝነት ለእግዚአብሔር ክብር በቅድስና መኖር እንደሚገባቸው ያምናል፡፡ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ብቻ የሚደረግ እግዚአብሔር የቀደሰው መሆኑን እና የአንድ ሥጋ ኪዳን እና የማይፈርስ ጥምረት ሆኖ በእግዚአብሔር እንደተጀመረ እናምናለን እናስተምራለን፡፡

(ዘፍ2:20-25 ማቴ19፥3-9)

Our Teachings

Scroll to Top